ጥያቄ እንጠይቅ፤ ተገቢውን እና ትክክለኛውን ጥያቄ። ለጊዜው ማድረግ የምንችለው፤ ግን ደግሞ ሁልጊዜም ማድረግ የሚገባን ይህንኑ ነው። ተገቢውን ጥያቄ ሳያቋርጡ መጠየቅ። ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ ሃገራችን ለምን ከአለማችን ድሃ አገራት ተርታ ተሰለፈች? ለምን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ካላደጉና ካልሰለጠኑ ቀዳሚዎቹ የአለማችን አገራት ጎራ ተገኘች? ለምን “ዜጎቿ” ለጋራ ጥቅም፣ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ እድገትና ብልጽግና መተባበር፣ መደማመጥና መግባባት የተሳነን የጥንታውያኑን የባቢሎንን ሰዎች አይነት ሆነን ተገኘን? ለምን ተፈጥሯዊ የሆነውን ክፉና ደጉን እንኳን መለየት ተሳነን? ዘርና ጎሳን መሰረት ያደረገውን የፖለቲካ ስርአት እንዴት ልንቀበል ቻልን? መሪዎቻችን ለምን አርቆ ማየት ተሳናቸው? የእኛስ እንደማህበረሰብ ከመጣው ገዢ ሁሉ ጋር በፍቅር የመክነፋችንንስ ነገር ምን እንበለው ይሆን?...ጥያቄው ይቀጥላል። ችግር የትዬለሌ በሆነበት ቦታና ሀገር ጥያቄውም የትየለሌ ቢሆን አይገርምም። ለመፍትሄ ፈላጊውና ነገር ግድ ለሚለው ለሃገር ተቆርቋሪው ለምን እና እንዴት ብሎ መጠየቁ ወደ መፍትሄው የሚያንደረድረው ድልድይ ሆኖ ያገለግለዋልና አብዝቶ ይጠይቅ። እኔም የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ፤ በሀገር ደረጃ እጅግ አሳሳቢ፣ ቀንደኛና ዋነኛ ተግዳሮት ናቸው ብዬ ያሰብኳቸውን መሰረታዊ ችግሮች ልናውቃቸው ይገባሉ ስል በበዕሬ ልከትባቸው ወሰንኩ። ሀገራችን አሁን ላለችበት የጨለማ ዘመን ውድቀት፣ የማህበረሰባችን የሞራል ልዕልናው መኮላሸትና መላሸቅ መንስኤው ምን እንደሆነ በቅደም ተከተል እያነሳሁ በማስረጃ እሞግታለሁ፤ እተቻለሁ። መፍትሄ የምለውንም እንደ አስፈላጊነቱ እጠቁማለሁ። ችግሮቻችንን የማለባበስና ሸፋፍኖ የማለፍ ልማድ ያለን ህዝቦች በመሆናችን እንደዚህ ላሉ ዝነኛ ላልሆኑ፤ ላልተለመዱና አከራካሪ (controversial) ለሆኑ ፅሁፎች ትኩረት ባንሰጥም፤ የማንሸራሽረው ዋናው ሃሳብ ግን የወደፊት እንደሃገርም ሆነ እንደግለሰብ የመቀጠል እድላችንን የሚወስን ብርቱ ጉዳይ በመሆኑ በእርጋታና በስክነት በማስተዋልም ጭምር እንዲነበብ ሲል ጸሃፊው በብዙ አክብሮት ከወዲሁ አንባቢያንን ያሳስባል።